መሪነት (Leadership)

መሪነት (Leadership)

#መሪነት (#Leadership)!!

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል አቅም ግንባታና ፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ፕሮፌሰር ታከለ ታደሰ #የመሪነት_መሰረታውያን (#Leadership) በተመለከተ ለተቋሙ አመራሮች ገለጻ ሰጡ!!


/ ታከለ በገለጻቸው፦#መሪነት ከባድ ኃላፊነት እና ፈተና መሸከም መሆኑን ተናግረው፤ እውነተኛ መሪ በደስታ ጊዜ ብቻ ሳይሆን በከባድ ፈተና ጊዜ ሁሉ በህዝብ ፊት በመቆም ችግሮችን የሚቀበል እና ለችግሮች መፍትሔ የሚያበጅ፣ ራሱን ከሕዝብ ጋር እኩል የሚያይ፣ በማንኛውም ጉዳይ ከሕዝቡ ጋር በጽናት የሚቆም፣ ህብረተሰቡን የሚያዳምጥ፣ ህዝብን እንደ ባለ አደራ የሚጠብቅ እና ተልዕኮውን በትዕግስት የሚፈጽም መሆኑን አመላክተዋል።

አክለውም ብቁ መሪነት ኃላፊነቱን በተጠያቂነት የሚወጣ፣ የህብረተሰቡን ደህንነት በመጠበቅና በማስተዋወቅ የሚሰራ፣ አሉባልታ፣ ወሬዎች እና ትችት እንደ መልካም አጋጣሚ ተጠቅሞ ለውጥ እና ዕድገት ለማስመዝገብ የሚሰራ፣ ለተችት እና አሉባልታ ቦታ ሳይሰጥ ያነገበውን ራዕይ እውን ለማድረግ ብቻ የሚተጋ መሆኑን ተናግረዋል።

"መሪነት በምሳሌ መምራት እንጂ በቃላት ማዘዝ አይደለም" ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፤ ለውጤታማ መሪነት ሥነ ተግባቦት በራስ መተማመን፣ ቁርጠኝነት፣ ፈጠራ (Creativity) እንዲሁም ባህሪ/ሰብዕና (Character) መሠረታዊ ብቃቶች መሆናቸውን አሳውቀዋል።

#ቅንነት (Integrity) #ታማኝነት እና የሞራል ልዕልና የአመራር ሁሉ መሠረት መሆኑን የተናገሩት ፕሮፌሰር ታከለ፤ የሌሎችን ፍላጎት እና ጥቅም ማስቀደም መቻል የአገልጋይነት ጥግ መሆኑን በመግለጽ የመሪነት እውነተኛ ትርጉም የሚገኘው በአገልጋይነት ስሜት ውስጥ መሆኑን ገልጸዋል።

'ለመሪነት ዲሲፕሊን በጣም አስፈላጊና ወሳኝ ነው' ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፤ ትዉልድን ለመቅረፅና ለሚመሯቸው ሰዎች ምሳሌ ለመሆንም ጭምር ዲሲፕሊንን የተላበሰ መሪ መሆን ግዴታ እንደሆነም አመላክተዋል።

በዲሲፕሊን የተካኑ መሪዎች ለሌሎች ቅድሚያ በመስጠት፣ አስፈላጊ ጉዳዮች ላይ በማተኮርና ሌሎችን እና ድርጅቶቻቸውን ወደፊት የሚያራምዱ ውሳኔዎችን በመወሰን እና በመሰል ክህሎቶች የተካኑ እንደሆኑ የገለጹት ፕሮፌሰር ታከለ፤ ከዚህ በተጨማሪም በዲሲፕሊን የተካኑ መሪዎች ከዘመኑ ጋር አብረው የሚዘምኑ፣ ከለውጥ ጋር መላመድ የማይሳናቸው የመሻሻል ምሳሌዎች ናቸው ሲሉ ተናግረዋል።

#የመሪነት ዋነኛ መለኪያዎች፦ ውሳኔ መስጠት መቻሉ፤ ሰዎች በራሳቸው እንዲያምኑ ማበረታታቱ፤ ሃላፊነት መውሰድ መቻሉ፤ ተጽዕኖ ማምጣቱ እና በስተመጨረሻም ነገሮችን ጀምሮ መጨረስ መቻሉ እና ውጤት ማሳየቱ ናቸው ሲሉም ፕሮፌሰር ታከለ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

መሪ ተጽኖ ፈጣሪ የሆነ፣ ሰርቶ የሚያሳይ፣ ምሳሌ የሚሆን፣ የተናገረውን የሚፈጽም፣ የለውጥ አርአያ የሚሆን፣ የሚያዳምጥና አስተዋይ፣ ለማንኛውም ውሳኔ የማይቸኩል እንዲሁም ሚዛናዊ አስተሳሰብ ያለው፣ ሰዎችን መረዳት የሚችል፣ውሳኔ የመወሰን አቅም ያለው፣ በጋራና በተናጠል በመስራት ስኬት የሚያስመዘግብ እና እውቀትና ጥበብ ያለው ሰው  ነው ሲሉም ዋና ዳይሬክተሩ አብራርተዋል።

ከራስ ወዳድነት አጥር በመውጣት ተቋም ወይም በዙሪያህ ያሉ ሰዎችን ማገዝና ማብቃት ከቻልክ የመሪነት ጉዞህ የተቃና ይሆናል ያሉት ፕሮፌሰር ታከለ፤ መሪነት ተቋምን ወይም የሰዎችን ህይወት እንዴት እቀይራለሁ ብሎ ማሰብ እንጂ እኔ ምን አገኛለሁ ብሎ ማሰብ አይደለም ሲሉ በገለጻቸው ጠቁመዋል።

መሪ፦ የሚመራውን አካል ጠንካራ ጎኑን ጠንቅቆ የሚያውቅና የሚያግዝ መሆኑን የገለጹት ፕሮፌሰር ታከለ፤ ከራስ ምቾት በመላቀቅ ሁለንተናውን አምኖ ለሰጠ ማህበረሰብ ታማኝና ቅን አገልጋይ በመሆን ለሌሎች ድልድይ መሆን ተገቢ ነው ብለዋል።

ኢንስቲትዩቱ በቀጣይ የመሪነት_መሰረታውያን (#Leadership) ላይ ትኩረት ያደረጉ የአቅም ግንባታ ስልጠናዎችን ለመስጠት እቅድ በመያዝ እየሰራ እንደሚገኝ እንዲሁም በዘርፉ የስልጠናና የማማከር አገልግሎት የሚሰጥ መሆኑን ከወዲሁ ለማሳወቅ እንወዳለን።